የጤና መድህን: የሚሸፍነው ምንድን ነው?

የጤና መድህን ሽፋን ካለዎ የአእምሮ ሰላምም አብሮ ይኖርዎታል። ድንገተኛ የጤና ችግር ቢደርስብዎ ወይም ወደ ሆፒታል መሄድ ቢኖርብዎ ከኪስዎ ብዙ ገንዘብ መክፈል አይጠበቅብዎትም። ወደ ዶክተር ሲሄዱ ያን ያህል ብዙ ገንዘብ መክፈል አይጠበቅብዎትም። ለመድሃኒቶችዎ ያን ያህል ብዙ ገንዘብ መክፈል አይጠበቅብዎትም። ሁሉም የጤና መድህን ሽፋኖች ተመሳሳይ ነገሮችን ስለማይሸፍኑ የጤና መድህን ሽፋንዎን ጥቅማ ጥቅሞችና የትኛዎቹ አገልግሎቶች እንደተሸፈኑ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

በሜሪላንድ ውስጥ ሁሉም የግል የመድህን ሽፋን እቅዶች ለተወሰኑ መሰረታዊ አገልግሎቶች መክፈል አለባቸው – እነዚህም ወሳኝ የጤና ጥቅማ ጥቅሞች ይባላሉ። በእነዚህ ወሳኝ የጤና ጥቅማ ጥቅሞች ውስጥ የተወሰኑ ገደቦች አሉ። ለምሳሌ ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ በትዕዛዝ የሚወሰዱ መድሃኒቶች አሉ። የኢንሹራንስ ድርጅቱ አንዱን መድሃኒት ሸፍኖ አንዱን ላያካትት ይችላል። ስለዚህ ዶክተርዎ አንድ መድሃኒት ካዘዘልዎ ኢንሹራንስዎ የሚከፍልላቸው መድሃኒቶች ዝርዝር ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው—ይህ ዝርዝር ፎርሙላሪ (formulary) ይባላል።ሌላው ምሳሌ ምርመራዎች ናቸው። የላብራቶሪ ምርመራዎች በሁሉም ኢንሹራንሶች የሚሸፈኑ ናቸው። ነገር ግን የኢንሹራንስ ድርጅትዎ ለተወሰኑ ምርመራዎች የሚከፍለው በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል።

 

ወሳኝ የጤና ጥቅማ ጥቅሞች

 • ዶክተርን መጎብኘት
 • በሃኪም ቤት ተኝቶ መታከም
 • ድንገተኛ የጤና አገልግሎት
 • የእናትና አዲስ የተወለዱ ህጻናት የጤና እንክብካቤ
 • የህጻናት የጤና አገልግሎት
 • ለህጻናት የጥርስ ሃኪምን መጎብኘት
 • ለህጻናት የአይን እንክብካቤ
 • በትእዛዝ የሚሸጡ መድሃኒቶች
 • የላብራቶሪ ምርመራዎች
 • የአእምሮ ጤና ህክምና
 • የአደንዛዥ እጽ አለአግባብ መጠቀም እንክብካቤ
 • የመከላከል ህክምና/ምርመራዎች (ያለምንም ተጨማሪ ወጪ)
 • የበሽታዎች ክትትል (ያለምንም ተጨማሪ ወጪ)

የኢንሹራንስ ድርጅትዎ ለየትኛዎቹ ህክምናዎች እነደሚከፍል እንዴት ማወቅ ይችላሉ? የትኛዎቹ ህክምናዎች፣ ምርመራዎች እና መድሃኒቶች እንደሚሸፈኑ ለማወቅ በኢንሹራንስ ካርድዎ ላይ ወዳለው የአባላት አገልግሎት ቁጥር ይደውሉ። ይህ ማንኛውንም ከባድ ወይም ውድ ህክምናዎች ከማድረግዎ በፊት መውሰድ ያለብዎት ወሳኝ እርምጃ ነው።

አንድ ህክምና ምን ያህል ወጪ እንደሚያስወጣ እንዴት ማወቅ ይችላሉ? በሜሪላንድ ውስጥ የሁሉም የህክምና ሂደቶች ወጪ የሚተመነው በመንግስት ኤጀንሲ ነው። አንድ ህክምና እርስዎን የሚያስወጣዎት ወጪ በኢንሹራንስ እቅድዎ ውስጥ ባለው የጋራ-ክፍያ (co-pay ) እና የጋራ-ኢንሹራንስ (co-insurance) ላይ እንዲሁም ተቀናሽ ክፍያዎን (deductible) ማሟላትዎ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ ርዕስ ላይ ቪዲዮ ለመመልከት www.DestinationHealth.me ድረ ገጽን ይጎብኙ ወይም የገንዘብ ጉዳይ የሚለውን ክፍል ያንብቡ።